አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

ሙሴ በተራራው ላይ

ሙሴ ናባው ተራራ ይወጣል፤ አብም የማይገባባትን ምድር ሁሉ ያሳየዋል። በመቶ ሃያ ዓመቱ ዓይኑ ሳይፈዝ በዚያ ይሞታል፤ አብም ማንም በማያውቀው ስፍራ ይቀብረዋል። እስራኤል ሠላሳ ቀን ያለቅሳሉ። ከዚያ ወዲህ አብ ፊት ለፊት ያወቀው እንደ እርሱ ያለ ነቢይ አልተነሣም።

ምዕራፍ 34።

ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ ተነሥቶ ኢያሪኮን ወደሚመለከተው ወደ ናባው ተራራ፣ ወደ ጲስጋ ጫፍ ወጣ፤ አባታችንም ምድሪቱን ሁሉ አሳየው፦ ከገለዓድ እስከ ዳን፣ ንፍታሌምን ሁሉ፣ የኤፍሬምንና የምናሴን ምድር፣ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ የይሁዳን ምድር ሁሉ፣ ኔጌብን፣ ሜዳውንም፦ የዘንባባ ከተማ የሆነችውን የኢያሪኮን ሸለቆ፣ እስከ ዞዓር አሳየው።

አባታችንም እንዲህ አለው፤ “‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’ ብዬ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማልኩላት ምድር ይህች ናት። በዐይንህ እንድታያት አድርጌአለሁ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ አትሻገርም።”

የአባታችን አገልጋይ ሙሴም አባታችን እንዳለው በሞዓብ ምድር በዚያ ሞተ። አባታችንም ቤትፌጎርን በሚያስተያየው በሞዓብ ሸለቆ ቀበረው፤ የመቃብሩን ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የሚያውቅ የለም። ሙሴ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበር፤ ዐይኖቹ አልፈዘዙም፣ ጕልበቱም አልጠፋም። የእስራኤል ልጆችም የልቅሶውና የሐዘኑ ቀኖች እስኪፈጸሙ ድረስ ሙሴን በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን አለቀሱለት። ሙሴ እጆቹን ጭኖበት ስለ ነበር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብ መንፈስ ሞልቶበት ነበር። የእስራኤልም ልጆች ሰሙት፣ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። ከዚያም ወዲህ አባታችን ፊት ለፊት እንደ ዐወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ በእስራኤል አልተነሣም፤ ይህም አባታችን በግብፅ፣ በፈርዖንና በሎሌዎቹ ሁሉ፣ በምድሩም ሁሉ ላይ እንዲያደርግ ስለ ላከው ስለ ምልክቶቹና ስለ ድንቆቹ ሁሉ ነው፤ ሙሴም በእስራኤል ሁሉ ዐይን ፊት ስላደረገው ስለ ብርቱ እጁ ሁሉ፣ ስለ ታላቁም የሚያስፈራ ሥራ ሁሉ ነው።