አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

አጽናኝ የሌለው እንባ

ሰባኪው አጽናኝ የሌለውን ግፍ አይቶ ሙታን ከሕያዋን ይሻላሉ ይላል። አብዛኛውን ሥራ የሚገፋው ቅንዓት ነው። ሆኖም ሁለት ከአንድ ይሻላሉ፤ ስትወድቅ የሚያነሣህ፣ የሚያሞቅህ፣ ከጎንህ ጸንቶ የሚቆም ይኖራልና። ተወዳጅ ንጉሥም እንኳ ብዙም ሳይቆይ ተፈላጊነቱን ያጣል።

ምዕራፍ 4።

እንደ ገና ተመለከትሁ፤ ከፀሐይ በታች የሚፈጸመውን በደል ሁሉ አየሁ፤ የተጨቈኑት በእንባ ነበሩ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ጨቋኞቻቸው ኀይሉን ይዘው ነበር፤ አሁንም አጽናኝ አልነበራቸውም። ስለዚህ ቀድሞ የሞቱት ሙታን፣ ገና በሕይወት ካሉት ሕያዋን ይልቅ ደስተኞች እንደሆኑ ተናገርሁ። ከሁለቱም ይልቅ ገና ያልተወለደው፣ ከፀሐይ በታች የሚደረገውን ክፋት ያላየው ይሻላል። ድካምና ብልኀት ሁሉ ከአንዱ ባልንጀራ በሌላው ላይ ከሚቀናው ቅናት እንደሚመነጭ አየሁ። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስን እንደ መከተል ነው። ሞኙ እጁን አጣጥፎ ራሱን ያጠፋል። በጸጥታ የሆነ አንድ እፍኝ፣ በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይሻላል።

እንደ ገና ከፀሐይ በታች ከንቱ የሆነ ነገር አየሁ፦

ብቻውን የሆነ ሰው አለ፤ ጓደኛ፣ ልጅ ወይም ወንድም የለውም፤ ድካሙ ፍጻሜ የለውም፤ ዐይኖቹም በሀብት አይጠግቡም። “ለማን እደክማለሁ?” ብሎ ይጠይቃል፤ “ራሴንስ ከመልካም ነገር ለምን እከለክላለሁ?” ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ክፉ ድካም ነው።

ሁለት ከአንድ ይሻላሉ፤ ለድካማቸው መልካም ዋጋ ያገኛሉና፦ አንዱ ቢወድቅ፣ ሌላው ያነሣዋል። ብቻውን ለሚወድቀው ግን ወዮለት፤ የሚያነሣው የለውምና። ደግሞም ሁለት ሆነው አብረው ቢተኙ፣ ይሞቃቸዋል። ብቻውን የሆነ ግን እንዴት ይሞቀዋል? ብቻውን የሆነ ይሸነፋል፤ ሁለት ሆነው ግን ይቋቋማሉ። ባለ ሦስት ፈትል ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም።

ጥበበኛው ጐበዝና ሞኙ ንጉሥ

ድኻ ቢሆንም ጥበበኛ የሆነ ጐበዝ፣ ሽማግሌ ከሆነና ከእንግዲህ ማስጠንቀቂያን መቀበል ከማያውቅ ሞኝ ንጉሥ ይሻላል። ጐበዙ ሊነግሥ ከእስር ቤት ወጥቶ መጥቶ ሊሆን ይችላል፤ ወይም በዚያው መንግሥት ውስጥ ድኻ ሆኖ ተወልዶ ሊሆን ይችላል። ከፀሐይ በታች የሚኖሩትን ሕያዋን ሁሉ፣ የንጉሡ ምትክ የሆነውን ጐበዝ ሲከተሉ አየሁ። በፊቱ የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ቍጥር የላቸውም ነበር። ከኋላ የመጡት ግን በእርሱ ደስ አልተሰኙም። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስን እንደ መከተል ነው።