አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

የሜዳ አህያን ነጻ ያወጣ ማን ነው?

ጥያቄው የሰው አስተዳደር በማያስፈልጋቸው የዱር ፍጥረታት ይቀጥላል፤ ብቻቸውን የሚወልዱ የተራራ ፍየሎች፣ ከተማን የሚንቅ የዱር አህያ፣ እንቁላሎቿን የምትረሳ ሰጎን፣ በፍርሃት የሚስቅ ፈረስ፣ በገደሉ ላይ ያለ ንስር። ከእነዚህ አንዳቸውም ለኢዮብ ምቾት የሚኖሩ አይደሉም።

ምዕራፍ 39።

“የተራራ ፍየሎች መቼ እንደሚወልዱ ታውቃለህ? ዋላዎች ሲወልዱ ትጠብቃቸዋለህን? ፅንሳቸውን የሚሸከሙባቸውን ወራት መቍጠር ትችላለህን? የሚወልዱበትንስ ጊዜ ታውቃለህን? ተንበርክከው ይወልዳሉ፤ የምጥ ሥቃያቸውም ያልፋል። ልጆቻቸው በሜዳ ላይ ይጠነክራሉ፤ ይሄዳሉ፣ ተመልሰውም አይመጡም።

“የሜዳ አህያን ነጻ ያወጣ ማን ነው? የፈጣኑን አህያ ገመድ የፈታስ ማን ነው? ለመኖሪያው ምድረ በዳውን፣ ለማደሪያውም የጨው ሜዳውን የሰጠሁት ለማን ነው? የከተማውን ጫጫታ ይንቃል፤ የነጂንም ጩኸት ከቶ አይሰማም። ለግጦሹ ተራሮችን ይዞራል፤ አረንጓዴውን ሁሉ ይፈልጋል።

“የሜዳ በሬ ሊያገለግልህ ይፈቅዳልን? በግርግምህ አጠገብ ያድራልን? የሜዳውን በሬ በገመድ ከትልም ጋራ ማሰር ትችላለህን? ሸለቆዎችንስ ተከትሎህ ያርሳልን? ኀይሉ ታላቅ ስለ ሆነ በእርሱ ትመካለህን? ድካምህንስ ለእርሱ አደራ ትሰጣለህን? እህልህን መልሶ እንዲያመጣ፣ ወደ አውድማህም እንዲሰበስብልህ ታምነዋለህን?

“የሰጎን ክንፎች በደስታ ይማታሉ፤ ነገር ግን የሽመላ ላባና ክንፍ ናቸውን? እንቍላሎቿን በመሬት ላይ ትተዋለች፤ በትቢያ ውስጥም እንዲሞቁ ታደርጋለች፤ እግር ሊጨፈልቃቸው እንደሚችል፣ የዱር አውሬም ሊረግጣቸው እንደሚችል ረስታ። ልጆቿ የራሷ እንዳልሆኑ፣ በጭካኔ ትይዛቸዋለች፤ ድካሟ ከንቱ ስለ መሆኑ ፍርሃት የላትም፤ ጥበብን እንድትረሳ ስላደረግኋት፣ ማስተዋልንም ስላላካፈልኋት ነው። ነገር ግን ለመሮጥ ስትነሣ፣ ፈረሱንና ጋላቢውን ትሥቃለች።

“ለፈረስ ኀይልን የምትሰጠው አንተ ነህን? አንገቱንስ በተንዠረገገ ጋማ ታለብሰዋለህን? እንደ አንበጣ ዘልሎ እንዲሄድ ታደርገዋለህን? ኵራት የተሞላበት ማናፈሱ ያስደነግጣል። መሬቱን በኰቴው እየጫረ በኀይሉ ይደሰታል፤ ወደ ውጊያም ይገሠግሣል። ፍርሃትን ይሥቃል፣ አይደነግጥምም፤ ከሰይፍም ፊት ወደ ኋላ አያፈገፍግም። አፎቱ በጐኑ ያንቃጭላል፤ የሚያብለጨልጨው ጦርና ዠምቢያም እንዲሁ። በጽኑና በሚንቀለቀል ስሜት መሬቱን ይውጣል፤ መለከት በተነፋ ጊዜ ጸጥ ብሎ መቆም አይችልም። መለከት በተነፋ ጊዜ፣ ‘እሰይ!’ ይላል፤ የውጊያውንም ሽታ ከሩቅ ያሸታል፤ የአዛዦችን ነጐድጓድና የጦር ጩኸት።

“ጭልፊት የሚበረው፣ ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ማስተዋል ነውን? ንስር ከፍ ብሎ የሚበረው፣ ጎጆውንም በከፍታ ላይ የሚሠራው በአንተ ትእዛዝ ነውን? በገደል ላይ ይኖራል፤ ማደሪያውንም እዚያ ያደርጋል፤ በዓለት አቀበት ላይ፣ በጽኑ መጠጊያው። ከዚያ ሆኖ ምግቡን ይፈልጋል፤ ዐይኖቹም ከሩቅ ያዩታል። ጫጩቶቹ ደምን ይጎነጫሉ፤ የተገደሉትም ባሉበት ስፍራ ሁሉ፣ እርሱ በዚያ ይገኛል።”