አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

ፍላጎቱ ለእኔ ነው

ሰውየው ጫማ ካጠለቁት እግሮቿ እስከ ጠጕሯ ድረስ ያመሰግናታል፤ በእርሷ በግልጽ ይደሰታል። እርሷ ይህን አትገፋውም። ፍቅሩ የጋራና የራሷም እንደ ሆነ ትናገራለች፤ ከዚያም ለእርሱ ፍሬ ወዳስቀመጠችበት ወደ ወይን ቦታዎችና ወደ መንደሮች ይዛው ትወጣለች።

ምዕራፍ 7።

በጫማ ውስጥ ያሉ እግሮችሽ እንዴት ውብ ናቸው፤ የመኳንንት ልጅ ሆይ! የጭኖችሽ ውበት እንደ ጌጥ፣ የተዋጣለት ባለሙያ እጅ ሥራ ነው። እምብርትሽ የተቀላቀለ ወይን የማይታጣበት ክብ ጽዋ ነው። ሆድሽ በአበቦች የተከበበ የስንዴ ክምር ነው። ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለት ግልገሎች፣ እንደ ዋላ መንታዎች ናቸው። አንገትሽ ከዝሆን ጥርስ እንደ ተሠራ ግንብ ነው። ዓይኖችሽ በባትረቢም በር አጠገብ ያሉ በሔሽቦን ኩሬዎች ናቸው። አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው። ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ዘውድ ሆኖሻል፤ የተንዠረገገ ጠጕርሽ እንደ ሐምራዊ ነው፤ ንጉሥ በዘለላው ተማርኳል። ፍቅሬ ሆይ፣ በደስታሽ ሁሉ እንዴት ውብ፣ እንዴትስ ደስ የምታሰኝ ነሽ! ቁመትሽ እንደ ዘንባባ ዛፍ ነው፣ ጡቶችሽም እንደ ዘለላዎቹ ናቸው። እንዲህ አልሁ፤ “ዘንባባውን ዛፍ እወጣለሁ፣ ፍሬውንም እይዛለሁ።” ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላዎች ይሁኑ፣ የትንፋሽሽም መዓዛ እንደ ፖም ይሁን፣ አፍሽም እንደ ምርጥ ወይን ይሁን። ለውዴ ለስለስ ብሎ ይፈስሳል፣ በከንፈርና በጥርስ ላይ ረጋ ብሎ ይንሸራተታል።

እኔ የውዴ ነኝ፣ ፍላጎቱም ለእኔ ነው። ውዴ ሆይ፣ ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ፣ በመንደሮችም እናድር። ማለዳ ወደ ወይኑ ተክል እንሂድ፤ የወይኑ ተክል ማቆጥቆጡን፣ አበቦቹ መፍካታቸውን፣ ሮማኖቹም ማበባቸውን እንይ። በዚያ ፍቅሬን እሰጥሃለሁ። ዱዳኢሞች መዓዛቸውን ይሰጣሉ፤ በበሮቻችን ላይም ውዴ ሆይ፣ ለአንተ ያከማቸኋቸው አዲሱና አሮጌው ምርጥ ፍሬዎች ሁሉ አሉ። a a v13 ዱዳኢሞች በጥንቱ ዓለም የፍቅር ፍላጎትን እንደሚቀሰቅሱና የመውለድ ኀይልን እንደሚያበረታቱ በሰፊው ይታመንባቸው የነበሩ መዓዛ ያላቸው ተክሎች ነበሩ።