አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

ፈጽሞ አለመርካት

ሰው ሀብት፣ ክብርና መቶ ልጆች ኖረውት ከእነዚህ በአንዱም እንዲደሰት ላይፈቀድለት ይችላል። ሰባኪው ከእርሱ ይልቅ ሞቶ የተወለደ ሕፃን የበለጠ ዕረፍት አለው ይላል። ምኞት ፈጽሞ አይጠግብም፤ ጥበብ ምንም ብልጫ አታስገኝም፤ ከዚያ በኋላ የሚሆነውንም ማንም አያውቅም።

ምዕራፍ 6።

ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤ በሰው ልጆችም ላይ እጅግ ይከብዳል፦ እግዚአብሔር ሀብትን፣ ብልጽግናንና ክብርን የሚሰጠው፣ ነፍሱ ከምትመኘውም ነገር ሁሉ ምንም የማይጐድልበት ሰው አለ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከዚህ እንዲበላ አይፈቅድለትም፤ በእርሱ ፈንታ መጻተኛ ይበላዋል። ይህ ከንቱ፣ የከፋ ደዌ ነው።

አንድ ሰው መቶ ልጆችን ቢወልድ፣ ብዙ ዓመታትም ቢኖር፣ ዕድሜው ምንም ያህል ረጅም ቢሆን፣ ነፍሱ ግን በመልካም ነገር ካልረካች፣ እርሱም ባይቀበር፣ ጨንግፎ የተወለደ ልጅ ከእርሱ ይሻላል እላለሁ። በከንቱ ይመጣል፤ ወደ ጨለማም ይሄዳል፤ ስሙንም ጨለማ ይሸፍነዋል። ፀሐይን ፈጽሞ ባያይ፣ ምንም ባያውቅም እንኳ፣ ከዚያ ሰው ይልቅ ዕረፍት አለው። ሺህ ዓመት ሁለት እጥፍ ቢኖር እንኳ፣ መልካምን ነገር ፈጽሞ ሳይደሰትበት ቢቀር፣ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ አይሄዱምን? የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፤ ምኞቱ ግን ከቶ አይጠግብም። ጠቢቡ ከሰነፉ የሚበልጥበት ጥቅም ምንድን ነው? ድኻውስ በሰዎች ፊት እንዴት መመላለስ እንዳለበት በማወቁ ምን ያተርፋል? ዐይን የሚያየው ከምኞት መንከራተት ይሻላል። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ያለው ሁሉ አስቀድሞ ስም ተሰጥቶታል፤ ሰውም ምን እንደ ሆነ ይታወቃል፤ ከእርሱ ከሚበረታም ጋር ሊከራከር አይችልም።

ቃላት በበዙ ቍጥር ከንቱነቱ ይጨምራል፤ ይህስ ለማንም ምን ይጠቅማል? እንደ ጥላ በሚያልፈው በከንቱ ሕይወቱ ጥቂት ዘመን ውስጥ፣ ለሰው መልካም የሆነውን ማን ያውቃል? ከእርሱ በኋላ ከፀሐይ በታች ምን እንደሚሆን ለሰው ማን ሊነግረው ይችላል?