አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

የዳዊት የመታደግ ጩኸት

የዳዊት ሺጋዮን፤ ስለ ብንያማዊው ኩሽ ለአባታችን የዘመረው።

በብንያማዊው በኩሽ የተከሰሰው ዳዊት ይምላል፦ ወዳጁን በክፉ መልሶ ከሆነ ጠላቱ ወደ ትቢያ ይርገጠው። ልብን የሚመረምረውን ፈራጅ አብን እንዲሠራ ይለምናል፤ ዓመፀኞችም በገዛ ጕድጓዳቸው ሲወድቁ ያያል።

ምዕራፍ 7።

አባቴ ሆይ፣ በአንተ እጠለላለሁ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ፤ ታደገኝም፤ እንደ አንበሳ ይዞ እንዳይበጣጥሰኝ፤ የሚያስጥልም ሳይኖር ቆራርጦ እንዳይጥለኝ። አባቴ ሆይ፣ ይህን ያደረግሁ እንደ ሆነ፣ በእጆቼም በደል ቢኖር፣ ለወዳጄ በክፉ የመለስሁ እንደ ሆነ፣ ወይም ጠላቴን ያለ ምክንያት የዘረፍሁ እንደ ሆነ፣ ያን ጊዜ ጠላት ያሳድደኝ፤ ይያዘኝም፤ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጥ፤ ክብሬንም በትቢያ ውስጥ ያኑር።

አባቴ ሆይ፣ በቍጣህ ተነሥ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ ተነሣ፤ ስለ እኔ ንቃ፤ ፍርድን አዝዘሃልና። የሕዝቦች ጉባኤ በዙሪያህ ይሰብሰብ፤ በእነርሱም ላይ በከፍታ ተቀመጥ። አባታችን ሕዝቦችን ይፈርዳል። አባቴ ሆይ፣ እንደ ጽድቄና በእኔ ውስጥ እንዳለው ቅንነት ፍረድልኝ። የክፉዎችን ክፋት አጥፋ፤ ጻድቁን ግን አጽና፤ አእምሮንና ልብን የምትመረምር ጻድቅ አባት ሆይ። ጋሻዬ ልበ ቅኖችን የሚያድን አባቴ ነው። አባታችን ጻድቅ ፈራጅ ነው፤ ዘወትርም የሚቈጣ አምላክ ነው። ማንም ንስሐ ባይገባ፣ አባታችን ሰይፉን ይስለዋል፤ ቀስቱን ገትሮ አዘጋጅቶታል። ገዳይ የጦር መሣሪያዎቹን አዘጋጅቷል፤ ፍላጻዎቹንም የሚንበለበሉ ፍላጻዎች ያደርጋል። እነሆ፣ ክፉው ሰው በክፋት ፀንሷል፤ ጣጣን ፀንሶ ውሸትን ይወልዳል። ጕድጓድ ይቈፍራል፤ ያሰፋዋልም፤ በሠራው ጕድጓድ ውስጥ ግን ይወድቃል። ጣጣው በራሱ ላይ ይመለሳል፤ ግፉም በራሱ አናት ላይ ይወርዳል። ስለ ጽድቁ አባቴን አመሰግናለሁ፤ ለልዑሉ አባቴ ስምም እዘምራለሁ።