አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

የንጉሡ የሰርግ ቀን

ሴቲቱ የምትወደውን በጨለማ ከተማ ውስጥ ትፈልገዋለች፤ ጠባቂዎቹን ትጠይቃለች፤ ከዚያም ታገኘዋለች፤ ወደ እናቷ ቤት እስክታስገባው ድረስ አትለቀውም። ከዚያም ሌሎች ድምፆች በጥበቃ የታጀበው የሰሎሞን ሠረገላ ሲቀርብ ይመለከታሉ፤ ንጉሡ በሠርጉ ቀን ዘውድ ደፍቶአል።

ምዕራፍ 3።

ሌሊቱን ሙሉ በመኝታዬ ላይ ነፍሴ የምትወደውን ፈለግሁት፤ ፈለግሁት፣ ነገር ግን አላገኘሁትም። አሁን ተነሥቼ በከተማይቱ እዞራለሁ፣ በመንገዶችና በአደባባዮች፤ ነፍሴ የምትወደውን እፈልጋለሁ። ፈለግሁት፣ ነገር ግን አላገኘሁትም። ጠባቂዎቹ ከተማይቱን ሲዞሩ አገኙኝ። “ነፍሴ የምትወደውን አይታችሁታልን?” ከእነርሱ አልፌ ገና ጥቂት እንደ ሄድሁ ነፍሴ የምትወደውን አገኘሁት። ያዝሁት፤ ወደ እናቴ ቤት፣ ወደ ጸነሰችኝ እናቴ ክፍል እስካገባው ድረስ አልለቀውም። የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች ሆይ፤ በሜዳ ባሉት ሚዳቋዎችና ዋላዎች አምላችኋለሁ፦ ፍቅር ራሱ እስኪፈቅድ ድረስ አታንቀሳቅሱት ወይም አትቀስቅሱት።

እንደ ጢስ ዐምዶች ከምድረ በዳ የሚወጣ፣ በከርቤና በዕጣን የታጠነ፣ በነጋዴው ሽቱ ዱቄቶች ሁሉ የታወደ ይህ ማን ነው? እነሆ፣ ይህ የሰሎሞን ገዛ አልጋ ነው፤ በዙሪያው ከእስራኤል ኀያላን የሆኑ ስድሳ ኀያላን ይከቡታል፤ ሁሉም ሰይፍ የያዙ፣ ለጦርነት የሠለጠኑ ናቸው፤ እያንዳንዱ የሌሊቱን ድንጋጤ ለመከላከል ሰይፉን በወገቡ ታጥቋል። ንጉሥ ሰሎሞን ከሊባኖስ ዕንጨት ለራሱ አልጋ ሠራ። ዐምዶቹን ከብር፣ መደገፊያውን ከወርቅ፣ መቀመጫውን ከሐምራዊ ጨርቅ አደረገ፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች በፍቅር ተለብጦ አጊጧል። የጽዮን ሴቶች ልጆች ሆይ፤ ውጡ፤ ንጉሥ ሰሎሞንን ተመልከቱ፤ በሰርጉ ቀን፣ ልቡ ደስ በተሰኘበት ቀን እናቱ ያቀዳጀችውን ዘውድ ደፍቷል።