አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው

አንድ ቀያሽ ኢየሩሳሌምን ሊለካ ይወጣል፤ እንዳይደክም ይነገረዋል፤ ከተማይቱ ከማንኛውም ቅጥር ተርፋ ትሞላለችና። አብ ራሱ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር፣ በውስጧም ክብር ይሆናል፤ ብዙ አሕዛብም ከእርሱ ጋር ይተባበራሉ፤ ልጆቹም ይሆናሉ።

ምዕራፍ 2።

ቀና ብዬ ስመለከት፣ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው አየሁ። እኔም፣ “ወዴት ትሄዳለህ?” ብዬ ጠየቅሁ። እርሱም፣ “ኢየሩሳሌምን ለመለካት፣ ስፋቷና ርዝመቷ ምን ያህል እንደ ሆነ ለማየት” አለኝ።

ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፤ ሊቀበለውም ሌላ መልአክ ወጣ፤ “ሩጥ፤ ይህን ጐበዝ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘በውስጧ ያሉት ሰዎችና እንስሳት እጅግ ስለሚበዙ፣ ኢየሩሳሌም እንደ ክፍት ሜዳ ትቀመጣለች።’ ” አለው።

“‘እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፤ ይላል አባታችን፤ በውስጧም ክብር እሆናለሁ።’ ”

“ኑ! ኑ! ከሰሜን ምድር ሽሹ፤ ይላል አባታችን፤ እንደ ሰማይ አራት ነፋሳት በትኜአችኋለሁና፤ ይላል አባታችን። ነዪ፣ ጽዮን ሆይ! ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋራ የምትኖሪ ሆይ፤ አምልጪ!

የሰማይ ሠራዊት አባት እንዲህ ይላል፤ ከክብሩ በኋላ የዘረፉአችሁን አሕዛብ ለመቃወም ላከኝ፤ የሚነካችሁ ሁሉ የዐይኑን ብሌን ይነካል፦

እነሆ፣ እጄን በእነርሱ ላይ አወዛውዛለሁ፤ ላገለገሉአቸውም ዘረፋ ይሆናሉ። የሰማይ ሠራዊት አባት እንደ ላከኝ ያን ጊዜ ታውቃላችሁ።

አንቺ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ ደስም ይበልሽ! እነሆ፣ በመካከልሽ ልኖር እመጣለሁና፤ ይላል አባታችን።

“በዚያን ቀን ብዙ አሕዛብ ከአባታችን ጋራ ይተባበራሉ፤ ልጆቼም ይሆናሉ። በመካከልሽ እኖራለሁ፤ የሰማይ ሠራዊት አባትም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂያለሽ። አባታችንም በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን ድርሻው አድርጎ ይወስዳል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደ ገና ይመርጣል።

ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአባታችን ፊት ዝም ይበል፤ ከተቀደሰ ማደሪያው ተነሥቶአልና።”