አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

በአምልኮና በሥርዓት ያለ ክብር

በጉባኤው ውስጥ ሁለት ችግሮች አሉ፦ ወደ አብ ሲጸልዩ ራስን መሸፈን ወይም አለመሸፈን፣ እንዲሁም ባለጠጎች ቀድመው ሲበሉ ድሆች የሚራቡበት የጌታ እራት። አንዳንዶች የደከሙትና የታመሙት በዚህ ምክንያት ነው፤ ሥጋውን ሳይለዩ ይበላሉና። እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።

ምዕራፍ 11።

እኔ ክርስቶስን እንደምመስል፣ እናንተም እኔን ምሰሉ።

በሁሉ ነገር ስለምታስቡኝና ወጎቹን ለእናንተ እንዳስተላለፍሁ ጠብቃችሁ ስለያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። ነገር ግን እንድታውቁ የምፈልገው ይህ ነው፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ አባታችን ነው። ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። ራሷን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ግን ራሷን ታዋርዳለች፤ ይህም ራሷ እንደ ተላጨ ነው። ሴት ራሷን መከናነብ እምቢ ካለች፣ ጠጕሯ ይቈረጥ፤ ነገር ግን ጠጕሯ መቈረጥ ወይም ራሷ መላጨት ለሴት ነውር ስለሆነ፣ ራሷን ትከናነብ። ወንድ የአባታችን መልክና ክብር ስለሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። ወንድ ከሴት አልመጣምና፤ ሴት ግን ከወንድ መጣች። ደግሞም ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረም፤ ሴት ግን ስለ ወንድ ተፈጠረች። ስለዚህ ሴት ስለ መላእክቱ በራሷ ላይ የሥልጣን ምልክት ሊኖራት ይገባል።

ሆኖም በጌታ ሴት ያለ ወንድ አትሆንም፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። ሴት ከወንድ እንደ መጣች፣ እንዲሁ ወንድ በሴት በኩል ይመጣል፤ ሁሉም ከአባታችን ነው። ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ራሷን ሳትከናነብ ወደ አባታችን ልትጸልይ ይገባታልን? ለወንድ ረጅም ጠጕር ውርደት እንደ ሆነበት ተፈጥሮ ራሱ አያስተምራችሁምን? ለሴት ግን ረጅም ጠጕር ቢኖራት ክብሯ ነው፤ ጠጕሯ መከናነቢያ እንዲሆናት ተሰጥቷታልና። ስለዚህ ነገር ለመከራከር የሚፈልግ ቢኖር፣ እኛ እንደዚህ ያለ ልማድ የለንም፤ የአባታችንም አብያተ ክርስቲያናት የላቸውም።

የጌታ ማዕድ ተዋረደ

ይህን ትእዛዝ ስሰጥ ግን፣ መሰብሰባችሁ ለክፉ እንጂ ለበጎ ስላልሆነ አላመሰግናችሁም። በመጀመሪያ፣ በማኅበር በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳለ እሰማለሁና፤ ከፊሉንም አምናለሁ። በመካከላችሁ ያሉት እውነተኞች ይገለጡ ዘንድ፣ መለያየት በመካከላችሁ ሊኖር የግድ ነውና። እንግዲህ በአንድ ቦታ ስትሰበሰቡ፣ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም። ስትበሉ እያንዳንዱ የራሱን እራት አስቀድሞ ይበላልና፤ አንዱ ይራባል፣ ሌላውም ይሰክራል። የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የአባታችንን ማኅበር ትንቃላችሁ፣ የሌላቸውንም ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? ላመስግናችሁን? በዚህ ነገር አላመሰግናችሁም።

እኔ ለእናንተ ያስተላለፍሁትን ከጌታ ተቀብዬአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት እንጀራ አንሥቶ፣

አመስግኖም ቈረሰውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ እኔን ለማሰብ ይህን አድርጉ” አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ እኔን ለማሰብ ይህን አድርጉ” አለ።

ይህን እንጀራ በበላችሁና ይህን ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

ስለዚህ ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ ባልተገባ ኹኔታ የጠጣ ሁሉ፣ የጌታ ሥጋና ደም በደለኛ ይሆናል። ሰው ራሱን ይፈትን፣ ከዚያም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ። ሥጋውን ሳይለይ የሚበላና የሚጠጣ ሁሉ፣ በራሱ ላይ ፍርድን ይበላል ይጠጣልና። ስለዚህ ከእናንተ ብዙዎች ደካሞችና ሕሙማን ናቸው፣ ብዙዎችም አንቀላፍተዋል። ራሳችንን ብንመረምር ኖሮ ግን፣ ባልተፈረደብንም ነበር። ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ፣ ከዓለም ጋራ እንዳንኰነን ይቀጣናል። ስለዚህ፣ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሆይ፣ ለመብላት በምትሰበሰቡ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። የተራበ ቢኖር፣ መሰብሰባችሁ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም በመጣሁ ጊዜ አስተካክላለሁ።