አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

እርሱን ማግኘት ብችል ኖሮ

ኢዮብ ጠብ ሳይሆን ፍርድ ቤት ይፈልጋል። እግዚአብሔር የሚኖርበትን ቢያገኝ ጉዳዩን አቅርቦ ነጻ ይወጣ ነበር። እግዚአብሔር ግን በምሥራቅም በምዕራብም የለም፤ የወደደውንም ያደርጋል። ኢዮብ እንደ ወርቅ ሆኜ እወጣለሁ ይላል፤ ሆኖም በፍርሃት እንደ ተሸበረ ይቀራል።

ምዕራፍ 23።

ኢዮብም መልሶ እንዲህ አለ፤ “ዛሬም ቢሆን ማማረሬ መራራ ነው፤ እያቃሰትሁም እጁ ከብዶብኛል። የት እንዳገኘው ባውቅ ኖሮ፣ ወደ መኖሪያውም በመጣሁ ነበር! ነገሬን በፊቱ ባቀረብሁ፣ አፌንም በመከራከሪያ በሞላሁ ነበር። የሚመልስልኝን ቃላት በተማርሁ፣ የሚነግረኝንም በተረዳሁ ነበር። በታላቅ ኀይሉ ይከራከረኝ ይሆንን? አይደለም፤ በርግጥ ያዳምጠኝ ነበር። በዚያ ቅን ሰው ከእርሱ ጋራ ይከራከር ነበር፤ በፈራጄም ለዘላለም ነጻ በወጣሁ ነበር። ነገር ግን ወደ ምሥራቅ ብሄድ፣ በዚያ የለም፤ ወደ ምዕራብም ብሄድ አላገኘውም። በሰሜን ሲሠራ አላየውም፤ ወደ ደቡብ ሲመለስ አላገኘውም። እርሱ ግን የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ በፈተነኝም ጊዜ እንደ ወርቅ ሆኜ እወጣለሁ። እግሬ ፈለጉን አጥብቆ ተከትሏል፤ መንገዱን ጠብቄ ፈቀቅ አላልሁም። ከከንፈሮቹ ትእዛዝ ፈቀቅ አላልሁም፤ የአፉን ቃላት ከዕለት እንጀራዬ አብልጬ አከብራለሁ። እርሱ ግን አይለወጥም፤ ማንስ ሊመልሰው ይችላል? የሚፈልገውን ሁሉ ያደርጋል። ለእኔ የወሰነውን ይፈጽማልና፤ እንደዚህ ያለ ብዙ ነገርም በልቡ አለ። ስለዚህ በፊቱ እደነግጣለሁ፤ ባሰብሁትም ጊዜ እርሱን እፈራለሁ። እግዚአብሔር ልቤን አስደክሞታል፤ ሁሉን ቻዩም አስደንግጦኛል። ይሁንና በጨለማ ዝም አልተባልሁም፤ ፊቴን በሚሸፍነው ጥቅጥቅ ጨለማም ዝም አልተባልሁም።”