አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል

ኢየሱስ በፊታቸው በድምፅ ይጸልያል። ሥራው እንደ ተፈጸመ ለአብ ይነግረዋል፣ እነዚህ ሰዎች በአብ ስም እንዲጠበቁና ከክፉው እንዲጋረዱ ይለምናል፣ በኋላም ለሚያምኑ ሁሉ አንድ እንዲሆኑ ይጸልያል።

ምዕራፍ 17።

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ አሻቅቦ ተመለከተ፤ እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል። ልጁ አንተን እንዲያከብር ልጅህን አክብረው፤ a a v1 ዮሐንስ 17 ኢየሱስ ለአብ ካቀረባቸው ጸሎቶች ሁሉ ተመዝግቦ የሚገኘው ረዥሙ ነው፤ ይህም ከመስቀሉ በፊት በነበረችው ሌሊት የተነገረ ሆኖ፣ አባት፣ ቅዱስ አባት፣ ጻድቅ አባት ብሎ ለሚጠራው ልቡን የከፈተበት ነው። ለሰጠኸውም ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ፣ በሰዎች ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። የዘላለም ሕይወት ይህች ናት፤ አንተን ብቸኛውን እውነተኛ አባት፣ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው። እንዳደርግ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ። አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋራ በነበረኝ ክብር አሁን ከራስህ ጋራ አክብረኝ።

ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁ። የአንተ ነበሩ፤ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። አሁን የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ ዐውቀዋል፤ የሰጠኸኝን ቃላት ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉ፤ ከአንተ ዘንድ እንደ መጣሁ በእውነት ዐወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አይደለም፤ ነገር ግን ስለ ሰጠኸኝ ስለ እነርሱ ነው፤ የአንተ ናቸውና። የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተውም የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። ከእንግዲህ በዓለም የለሁም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱ ደግሞ አንድ እንዲሆኑ፣ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋራ ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ በስምህ ጠበቅኋቸው። ጠበቅኋቸው፤ መጽሐፉም ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ አንድ እንኳ አልጠፋም። b b v12 “የጥፋት ልጅ” የሚለው ኢየሱስን አሳልፎ ለሰጠው ለአስቆሮቱ ይሁዳ የተሰጠ ስም ነው። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ደስታዬም በእነርሱ ዘንድ ተፈጽሞ እንዲገኝ ይህን በዓለም ሳለሁ እናገራለሁ። ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ እነርሱም ከዓለም ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው። ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም፤ ነገር ግን ከክፉው እንድትጠብቃቸው እለምናለሁ። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ እነርሱ ከዓለም አይደሉም። በእውነት ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ፣ እኔ ደግሞ እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። እነርሱ ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ስለ እነርሱ ራሴን እቀድሳለሁ።

ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም የምለምነው፤ ነገር ግን በቃላቸው በእኔ ስለሚያምኑትም ጭምር ነው። አባት ሆይ፣ አንተ በእኔ እኔም በአንተ እንዳለሁ፣ እነርሱ ሁሉ አንድ ይሁኑ፤ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሁኑ፤ ዓለምም አንተ እንደ ላክኸኝ ያምን ዘንድ ነው። እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ሆነህ፣ ፍጹም አንድ እንዲሆኑ፤ ዓለምም አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን እንደ ወደድኸኝ እነርሱንም እንደ ወደድህ ያውቅ ዘንድ ነው። አባት ሆይ፣ የሰጠኸኝ እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋራ እንዲሆኑ፣ ክብሬንም እንዲያዩ እወዳለሁ፤ ይህም ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝ ክብር ነው። ጻድቅ አባት ሆይ፣ ዓለም አያውቅህም፤ እኔ ግን ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ዐውቀዋል። ስምህን አስታወቅኋቸው፤ ወደ ፊትም አስታውቀዋለሁ፤ ይህም የወደድኸኝ ፍቅር በእነርሱ እንዲኖር እኔም በእነርሱ እንድኖር ነው።”