አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

ተላላ ተላላነቱን ይደግማል

የሦስት ዓይነት ሰዎች ዝርዝር ማለት ይቻላል። ሊከበር፣ ሊቀጠር ወይም ሊፈወስ የማይችል ሰነፍ፤ በር በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር በአልጋው ላይ የሚገላበጥ ታካች፤ ካቆሰለ በኋላ «እየቀለድሁ ነበር» የሚል አታላይ። ጕድጓድ የሚቈፍር ራሱ ይወድቅበታል።

ምዕራፍ 26።

በበጋ እንደሚወርድ በረዶ፣ በመከር ወቅትም እንደሚዘንብ ዝናብ፣ ክብር ለተላላ አይገባውም። እንደሚንፈራፈር ድንቢጥ፣ ወይም እንደሚበር ጨረባ፣ ያለ ምክንያት የተነገረ እርግማን አያርፍም። ለፈረስ አለንጋ፣ ለአህያ ልጓም፣ ለተላሎች ጀርባም በትር ነው። ለተላላ እንደ ተላላነቱ አትመልስለት፤ አለዚያ አንተ ራስህ እንደ እርሱ ትሆናለህ። ለተላላ እንደ ተላላነቱ መልስለት፤ አለዚያ በራሱ ዐይን ጥበበኛ ይሆናል። በተላላ እጅ መልእክት የሚልክ፣ የራሱን እግር ይቈርጣል፤ ዐመፅንም ይጠጣል። በተላላ አፍ ያለ ምሳሌ፣ እንደ ዐንካሳ ሰው ቅል እግር ነው። ለተላላ ክብርን መስጠት፣ በወንጭፍ ድንጋይን እንደ ማሰር ነው። በተላላ አፍ ያለ ምሳሌ፣ በሰካራም እጅ እንዳለ እሾኽ ነው። ተላላን የሚቀጥር ወይም ማንኛውንም መንገደኛ የሚቀጥር፣ ሁሉን እንደሚያቈስል ቀስተኛ ነው። ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ፣ ተላላም ተላላነቱን እንዲሁ ይደግማል። በራሱ ዐይን ጥበበኛ የሆነ ሰው ታያለህን? ከእርሱ ይልቅ ለተላላ ተስፋ አለው።

ሰነፍ ሰው፣ “በመንገድ ላይ አንበሳ አለ! በአደባባዩም አንበሳ አለ!” ይላል። በር በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፣ ሰነፍ ሰውም በዐልጋው ላይ እንዲሁ ይገላበጣል። ሰነፍ ሰው እጁን በወጭቱ ውስጥ ይከታል፤ ወደ አፉ መልሶ ለማምጣትም ይታክታል። ሰነፍ ሰው ጥበብ ባለው መልስ ከሚመልሱ ሰባት ሰዎች ይልቅ፣ በራሱ ዐይን ጥበበኛ ነው።

የራሱ ባልሆነ ጠብ ውስጥ ጣልቃ የሚገባ መንገደኛ፣ ውሻን ጆሮውን ይዞ እንደሚጐትት ነው።

የእሳት ችቦ፣ ፍላጻና ሞት እንደሚወረውር ዕብድ፣ ባልንጀራውን አታሎ፣ “ቀልጄ ነበር!” የሚል ሰው እንዲሁ ነው።

ዕንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ ሐሜተኛም ከሌለ ጠብ ይበርዳል። ከሰል ለፍም፣ ዕንጨትም ለእሳት እንደሚሆን፣ ጠበኛ ሰውም ጥልን እንዲሁ ያነድዳል። የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤ ወደ ሆድ ውስጥም ዘልቆ ይወርዳል።

ክፉ ልብ ያለው ለስላሳ ከንፈር፣ የሸክላ ዕቃን እንደሚሸፍን ብረቶ ነው። ጠላት በከንፈሩ ራሱን ይሰውራል፣ በልቡ ውስጥ ግን ተንኰልን ይሰበስባል። ለዛ ባለው ቃል ሲናገር አትመነው፤ ሰባት ርኵሰቶች ልቡን ሞልተውታልና። ጥላቻው በተንኰል ቢሰወርም፣ ክፋቱ በጉባኤ ፊት ይጋለጣል። ጒድጓድ የሚቈፍር ወደ እርሱ ይወድቃል፤ ድንጋይም የሚያንከባልለው ላይ ተመልሶ ይንከባለላል። ሐሰተኛ ምላስ የሚያደቅቃቸውን ይጠላል፤ አሞጋጋሽ አፍም ጥፋትን ያመጣል።