አሁን በኅትመት ይገኛል
መጽሐፍ

ምስጋና መዘመር እንዴት መልካም ነው

አብ ከዋክብትን ይቆጥራል፣ እያንዳንዳቸውንም በስም ይጠራል፤ ልባቸው የተሰበረውንም ይጠግናል። ውርጭንና በረዶን ይልካል፣ ከዚያም የሚያቀልጠውን ቃሉን ይልካል። ደስ የሚያሰኘው የፈረስ ኃይል ወይም የሰው ብርታት ሳይሆን በፍቅሩ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው።

ምዕራፍ 147።

ሃሌ ሉያ! ለአባታችን ምስጋና መዘመር እንዴት መልካም ነው፤ እርሱን ማመስገንም እንዴት ያማረና የሚገባ ነው።

አባታችን ኢየሩሳሌምን ይገነባል፤ የተበተኑትን የእስራኤልን ሕዝብ ይሰበስባል። ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል። ከዋክብትን ይቈጥራል፤ እያንዳንዳቸውንም በስም ይጠራቸዋል። ጌታ አባታችን ታላቅ ነው፤ በኀይሉም ብርቱ ነው፤ ማስተዋሉ ወሰን የለውም። አባታችን ትሑታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ክፉዎችን ግን ወደ መሬት ይጥላል።

ለአባታችን በምስጋና ዘምሩ፤ በበገና ዜማ አቅርቡለት። ሰማያትን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድር ዝናብን ያዘንባል፤ በኰረብቶች ላይ ሣርን ያበቅላል። ለእንስሳት መኖአቸውን ይሰጣል፤ ለሚጮኹ የቍራ ጫጩቶችም ይሰጣል። ደስታው በፈረስ ኀይል አይደለም፤ ተድላውም በሰው እግሮች ላይ አይደለም። የአባታችን ልብ እርሱን በሚፈሩት፣ በኪዳኑ ፍቅር ተስፋ በሚያደርጉት ደስ ይለዋል።

ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አባታችንን አመስግኝ! ጽዮን ሆይ፣ አባትሽን አመስግኝ! የደጆችሽን መወርወሪያዎች ያጠነክራልና፤ በቅጥርሽ ውስጥ ያሉትን ልጆችሽን ይባርካል። ለዳርቻዎችሽ ሰላምን ይሰጣል፤ በተመረጠ ስንዴ ያጠግብሻል። ትእዛዙን ወደ ምድር ይልካል፤ ቃሉም ፈጥኖ ይሮጣል። በረዶን እንደ ጥጥ ይሰጣል፤ ዐመዳይን እንደ ዐመድ ይበትናል። በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ይጥላል፤ በብርዱ ፊት ማን ሊቆም ይችላል? ቃሉን ይልካል፤ በረዶውንም ያቀልጣል፤ ነፋሱን ያናፍሳል፤ ውሃዎችም ይፈስሳሉ። ቃሉን ለያዕቆብ ይገልጣል፤ ሥርዐቱንና ፍርዶቹን ለእስራኤል ይነግራል። ለሌላ ለማንኛውም ሕዝብ እንዲህ አላደረገም፤ እነርሱም ፍርዶቹን አያውቁም። ሃሌ ሉያ!